ቅፅ_2_ቁጥር_10 | Page 7

ዶ / ር ቢኒያም ግርማቸው

አብርሆት

አራቱ በጎ ልማዶች

በማህበራዊ ግንኙነታችን ለሠዎች ምቹ ፀባይ ኖሮን በነፃነትና በግልፅነት የተሞላ ጤናማ ሕይወት መኖር እንድንችል ከሚረዱን ክህሎቶች መካከል የሚከተሉት ተጠቃሽ ናቸው ።
ቅንነት
በየቀኑ ልናከናውናቸው ከሚገቡና ማኅበራዊ ሕይወታችንን ለማሳደግ ከሚረዱን ተግባራት መካከል በቅንነት ስሜት ተሞልተን ሌሎችን መርዳት የመጀመሪያው በጎ ልማድ ነው ። ለምሳሌ ከተሣፈርንበት ታክሲ ስንወርድ ከፊታችን ለምትገኘው የልጆች እናት ቅድሚያ መስጠት ፣ ካፍቴሪያ ገብተን አገልግሎት ለምትሰጠን አስተናጋጅ በትህትና እና በፈገግታ የታገዘ ትዕዛዝ መስጠት ግንኙነታችንን ጤናማ ያደርገዋል ። በሠጠነው ነገር ልክ ከሌሎች ተገቢውን መልስ ባናገኝ እንኳን ትልቁ ቁም ነገር በየዕለቱ አንድ ሰው መርዳት ወይም ደስታ እንዲሰማው ማድረግ መቻላችን ነው ። እንዲህ አይነቱን ልማድ ስናዳብር በየዕለቱ በየትኛውም ሰው ሕይወት ላይ ተፅዕኖ መፍጠራችን ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ከማንም ጋር ተግባቢና ለሌሎች ምቹ የሆነ ስብዕና ይኖረናል ። እያንዳንዱን ሰው በፈገግታ ተሞልተን በቀረብነው መጠም ማንነቱን በግልፅ ለማሳየት ፈቃደኛ ሊሆን ስለሚችል ከድክመትና ጥንካሬው የምንማርባቸውን አጋጣሚዎችም እናገኛለን ።
አመስጋኝነት
እያንዳንዱ ሰው ከተፈጥሮ በየጊዜው ለሚያገኛቸው በጎ ሥጦታዎች ለፈጣሪው ምስጋና ማቅረቡ የተለመደ ነው ። በሰዎች ዘንድ እርስ በእርስ የመመሠጋገኑ ልማድ ግን በሚፈልገው መጠን የዳበረ አይመስልም በዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችን ስለ እኛ የሚጨነቁ መልካሙን ሁሉ የሚመኙልንና በጉብዝናችንም ወቅት አድናቆታቸውን የሚቸሩና በርካታ ሰዎች በዙሪያችን ይኖራሉ ። እነኚህን ሰዎች ልናመሰግናቸው ይገባል ። ምስጋና በቸርናቸው መጠን ግንኙነታችን እየጠነከረ ከመምጣቱ በተጨማሪ በውስጣችን ያለውን አዎንታዊ ስሜት የማሳደግ አቅም እናገኛለን ።
ከቤተሰባችን አባላት ከሥራ አጋሮቻችን ወይም በሆነ አጋጣሚ ከምናገኛቸው አዳዲስ ሰዎች ለሚደረግልን ድጋፍ ተገቢውን ምስጋና ከሠጠን ይህ በጎ ልማድ ተጨማሪ የሕይወት አጋዦች ማግኘት የምንችልበት ሌላ የግንኙነት በር ይከፍትልናል ።
ራሳችንን መውደድ
ራሳችንን በወደድንና በተቀበልን መጠን ለምናከናውናቸው ድርጊቶች ሁሉ የሌሎችን ይሁንታ ወይም ድጋፍ ለመጠበቅ መገደዳችንን ይቀራል ። ራሳችንን መቀበል መቻል በራስ መተማመናችንን የሚያሳድግ በመሆኑ ሃሳባችንን ለሌሎች ማጋራት ካስፈለገን እንኳን ምንም አይነት ፍርሃት አይሰማንም ለራሳችን መወደድ ሲጨምር የልባችንን መጋረጃ ገልጠን በሰዎች ፊት ብርሃናችን እንዲያበራና የተለየ ስብዕና እንዲኖረን በማድረግ እንሞክራለን ። ይህ ደግሞ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች በስብዕናችን እንዲሳቡና ምክንያት ይሆናል ። ራሳችንን በተገቢ መንገድ መወደድ ስንጀምር ተገቢውን ዋጋ ሊነፍጉን ከሚሹ ሰዎች በመራቅ በአስተሳሰብ በአመለካከት ከሚመስሉን ደስተኛና አዎንታዊ ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት እናሳድጋለን ። ( በዚህ ርዕስ ስር የተገለፀው ራስን መውደድ ሌሎችን ለመጉዳት ጥቅም ላይ ከሚውለው የራስ ወዳድነት ስሜት የተለየ መሆኑን ማስተዋል ተገቢ ነው ።)
ይቅር ባይነት
ከሰዎች ጋር ለመኖር እጅግ ጠቃሚ ከሆኑ ክህሎቶች መካከል አንዱ ይቅር ባይነት ነው ። ሰዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ስሜታችንን የሚጎዱ ወይም ጥቅማችንን የሚያስቀሩ ድርጊቶች ሊፈፅሙብን ይችላሉ ። እያንዳንዱን ድርጊት በአሉታዊ መንገድ ብቻ በመቀበል ግንኙነታችንን ከማቋረጥ ይልቅ በይቅር ባይነት ማለፍ የትልቅነት ምልክት ነው ። ምንጭ- ሰው ሁን ከሰውም ሰው ሁን የትስስር ገፅ የተወሰደ
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 7