ቅፅ_2_ቁጥር_10 | Página 6

ሀገሬ

እንቁ-ጣጣሽ እንቁ የሆነ አዲስ ተስፋን ፣ አዲስ ህሊና ፣ ያልተኖረ አመትን የሚሰጠን ከበዓላት ሁሉ እጅግ የላቀው በዓል ነው ፡፡ አዲስ አመት በሀገራችን ጅራፍ ከሚጮህበትና ሙልሙል ዳቦ ከሚቆረስበት የቡሄ በዓል ጀምሮ አሸንዳ ፣ ሻደይ ፣ አሸንድዬና ሶለልን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ልጃገረዶች ጨዋታ አጅቦ በመስከረም ወር በፈካው አደይ አበባ ደምቆ የሚገባ ብሩህ ወር ነው ፡፡ ከጭጋጋማው ፣ ብርዳማው ፣ የጤዛና የጭቃ ወራት ወደ ፈካው የፀሀይ ፣ የብሩህ ደመና ስንቅ ወደ ያዘው የመስከረም ወር የምንሸጋገርበት የተስፋ አመት ባለቤቶች ብንሆንም ዳሩ ግን ዛሬም እንደ ሀገር ነጭ ለብሰን የምንቀበለው አዲስ አመት ሳይሆን በየሜዳው ያልበረዱ ባሩዶች ፣ በአደይ ፋንታ የወጣቶች ደምና ስጋ የተዘረጋት መሬት ፣ ትናንት በአሸንዳ የቦረቁ እንስቶች ዛሬ በሰቀቀን ከሞቀው ጎጇቸው ወጥተው በጎዳና ላይ ተጠልለው ይገኛሉ ፡፡ ዛሬ ላይ እንደ ትናንቱ ገበሬው ዝናብ እየደበደበው ለም መሬቱን ከማረስ ይልቅ ዘመንን ባልዋጀ ትርጉም የለሽ ጸብ ጠመንጃ አንግቶ ተራራ ላይ ነው ፤ ዛሬ ለበዓሉ ድምቀት የሚሆኑ በሬዎችና ፍየሎች በበርሀ ላለው ወጥቶ-አደር ( ወታደር ) የዕለት ጉርስነት ይላካሉ ፣ ከሰው አልፎ እንሰሳትን ያዘመትንበት የአንድ እናት ልጆች ጸብ ለራሳቸው ምቾት ብቻ በሚጨነቁ ግለሰቦች አማካኝነት የነገ ተስፋቸውንና ምኞታቸውን ሰውተው በየበረሀው የሚወድቁ ወጣቶችን ያሳየናል ፡፡ አመት ቆጥረን በደልን መሻር ያቃተን ደካሞች ሆነናል ፣ ለይቅርታ የሚዘረጋ የማርያም ጣታችንን የጠመንጃ ቃታ እየሳብንበት ነው ፣ ትናንት ሻደይ ፣ አሸንዳንና ሶለልን በጋራ ያከበሩ የሰሜን ልጃገረዶች ዛሬ ተከፋፍለው በቄጤማ ፋንታ ጥይት በጀርባቸው አንግተው ከደስታ ይልቅ የሀዘን ሲቃ ይጋታሉ ፡፡ ደመናው ሸሽቶ ጸሀይ የምትወጣበት አደይ የምትፈካበት ወር እንደትናት የምንቦርቅበት ሳይሆን አንገት የምንደፋበት ነው ፡፡ ዘመን ሲለወጥ መለወጥ ያቀታን ለምን ይሆን ? ምድር ግዜ ጠብቆ ጭቃውን ደረቅ ክረምቱን በጋ ሲያደርገው የኛስ ልብ ክፋትን በይቅርታ ፣ ጥላቻን በፍቅር ፣ ጦርነትን በሰላም ፣ ጠብመንጃን በቄጤማ መለወጥ እንዴት አቃተው ? ከአለም የተለየነው በዘመን አቆጣጠር ወይስ ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር የራስ ባህል ጌጥ ማሳያ ፣ ታላላቅ አክባሪ ህዝቦች ብዙ ቀለም አንድ መልክ ያለን መሆናችን ነውን ? አዎ አመት ከመሻገር በዘለለ የምንመልሰው እልፍ ጥያቄ አለ ፣ በዓል ደርሶ ከምንቀይረው ልብስ ውጪ ልባችንን በቅንነት ኑሯችንን በምክንያታዊነት ዘመናችንን ሀገር ፍቅር አንጸን ልቀይር ይገባል ፡፡ አውዳመት አውዳሚ ከሆነው ትርጉም የለሽ ጸብ የምንርቅበት ሊሆን ግድ ይላል ፡፡ ቃታ የሳቡ እጆች ልባቸውን ለእርቅ እጃቸውን ለሰላም ይዘረጉ ዘንድ ሀገሬ ትጣራለች ፡፡ ለአዲስ አመት አዲስ ለብሰን ፣ ተስፋ ሰንቀን ፣ ፍቅር አኑረን ፣ መልካምነትን ተግብረን የምናከብረው ብቻ ሳይሆን አዲስ ስንለብስ ካለን ላይ ለተቸገሩት የምናካፍልበት ፣ በፍካት ስንስቅ በአዕምሯችን የተሞላውን ክፋት ፣ ዘረኝነት ፣ ጥላቻ ፣ ቂም ወደ ኋላ ጥለን እኛ ሞልቶ ተርፎን ጠግበን ስንደፋ ምንም የሚቀመስ ላላገኙ በየጎዳናው የወደቁትን የምናስብበት ዘመን ፣ የሀሳብ ፣ የኑሮ ፣ የትምህርት ፣ የህይወት መንገድ ለውጥ የምናደርግበት አመት መሆን ይገባዋል ፡፡ ውድ የሀገሬ አምድ አንባቢያንና የቅንድል ዲጂታል መጽሔት ቤተሰቦች በትናንት ቁርሾ ፣ በደል ፣ ቂም የነገን ብርሀን የምንቀበልበት ሳይሆን በፍቅር ፣ በአንድነት ፣ በመቻል ፣ በቅንነትና በህብረት የምንመራረቅበት ይሁንልን ፡፡ አዎ አሜን እያልን ሀገርን ፣ አሜን እያልን እማማን ፣ አሜን እያልን ጋሼን ፣ አሜን እያልን እታለምን ፣ አሜን እያልን የሰው ልጅን ሁሉ የምንመርቅበት እንዲሆን በምርቃት መጪውን ግዜ እንቀበል ፡፡ ተቀበይ
ሀገሬ ተራሮችሽ በአደይ ፣ ልጆችሽ በጸጋ ፣ መንደርሽ በደስታ የሚበሩበት አመት ያምጣልሽ ቃታ የሳቡ እጆች የማሪያም ጣታቸውን ለይቅርታ ይዘርጉልሽ ለጸብየምንዝርበት ሳይሆን ለሰላም የምጮህበት አንደት ለህዝቦችሽ ያድል ፡፡ አሜን በይ ሀገሬ ምድርሽን ከአደይ የበለጠ ምን አይነት አበባ ሊወክላት ይችላል ? ከመስከረም የበለጠ ወርስ ምን አለሽ ? በቢጫ ቀለም የያዘች ውብ አርንጓዴ ምድርሽን በቀይ ደም ተቦክቶ በተቀበረ መሬት የበቀሉ ልዩ ስጦታዎችሽ ናቸውና አሜን በይ ሀገሬ ፡፡ ውድ አንባያን መጪውን አመት በመተሳሰብ ፣ በመዋደድ ፣ በቅንነት ፣ በምክንያታዊነት ፣ በሀገር ፍቅር ደምቀን ራሳችንን ፣ ቤተሰባችንን ብሎም ሀገራችንን ኢትዮጲያ ወደ ሰላም የምናደርስበት ዘመን ያድርግልን እያልኩ የአዲስ አመት የሀገሬ አምድ ጽሁፌን አበቃሁ ፡፡ መልካም በዓል !

አንደ ምድሩ የፈካ ፣ እንደ ወራቱ ያበራ የሰላም ዘመን ያድርግልን ! ኢትዮጲያ ለዘላለም በህዝቦቿ ፍቅር ትኑር ...

ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 6