ሀገሬ
በሀይሉ ወ / ይፍራው ( መባ )
በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ የማኔጅመንት መምህርና ቢዝነስ ሪሰርቸር ethiomebreku3000 @ gmail . com
ሀገር እንቁ ጣጣሽ
ያሳር ክንድሽ አቅፎን !
አዲስ አመት ገባ እንዲህ እንደዋዛ ተፈጥሮ በውበት መንፈሴን ሳይገዛ ግን አዲስ ተስፋ ነው ዘመን ያልተኖረ ከአሳለፍነው በላይ በተስፋ የከበረ ፡፡
ግዜ እንደ ሀሳብ መስመር ለሰው ልጆች በቁጥር ተሰፍሮ የተሰጠ የመኖር ተስፋ ፣ የነገን ህይወት የትናንትን አሻራ የያዘ የዘመን ሀዲድ ላይ የተሰራ የተፈጥሮ ስጦታ ነው ፡፡ የግዜ አቆጣጠር የሰው ልጅ ተፈጥሮን ከማስተዋልና አጠቃላይ የጨረቃን ፣ የምድርን ፣ የፀሀይን እና የከዋክብት ቁርኝት በጥብቅ በመከታተል የቀመረው ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡ የሰው ልጅ በዙሪያው ያሉት የህዋ አካላትና የተፈጥሮ ወቅቶችን በመደበኛነት መቀያየር ተከተሎ የግዜ ቀመርን መበየን ችሏል ፡፡ ይህም የጨረቃን እንቅስቃሴ እንደዚሁም የምድርን ዙረት ተከትሎ የጀንበርን መጥለቅና መውጣት በጥልቀት ከማስተዋል የመነጨ ነው ፡፡ ሰዓታትን ወደ ቀናት ቀናትን ወደ ወራት ከዚያም ወደ አመታት አስልቶ በመቀመር የግዜ አቆጣጠርን መፍጠር ችሏል ፡፡ በዚህም መሰረት በአለም ላይ የጨረቃን ዙረት በመከተል የተቀመረ የግዜ አቆጣጠር ( lunae calendar ) በመባል የሚታወቅ ሲሆን ሌላኛው የምድርን በፀሐይ ዙሪያ መሽከርከር ተከትሎ የተቀመረው የፀሐይ የግዜ አቆጣጠር ( solar calendar ) በመባል ሲጠራ ሶስተኛው ቀመር እነዚህን ሁለት የግዜ አቆጣጠር አጣምሮ የተገኘው ( lunesolar calendar ) በመባል ይታወቃል ፡፡
ሰላም ውድ የቅንድል ዲጂታል መጽሔት ቤተሰቦችና የሀገሬ አምድ አንባብያን እንዴት ቆያችሁን ? ሳምንታቶቹ በስኬት ወሩ በውጤት የታጀበና የሚታል ስራ የሚጨበጥ ውጤት እንዳገኛችሁበት ተስፋ አለኝ ፡፡ በአዲስ አመት ልዩ ዕትም በሀገሬ አምድ ስለ ልዩ የሀገራችን ዘመን አቆጣጠር እና በእንቁ ተውቦ በጣጣ ታጅቦ በተስፋና በስጋት ፣ በፍርሀትና በምኞት ላይ ሆነን የምንቀበለውን አዲስ አመት ከተስፋችን ጋር በማያያዝ ላነሳ ወደድኩ ፡፡ አለም ላይ የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ያላቸው ሀገራት ፣ ብሔሮችና ጎሳዎች ያሉ ቢሆንም በዋነኝት አለም የሚያውቃቸው አራት እንደሆኑ በተለያዩ የሐይማትና የታሪክ መዛግብት ተጽፎ ይገኛሉ ፡፡ እነሱም ፡ - የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ፣ የአይሁዳውያን የዘመን አቆጣጠር ፣ የአረቦች ዘመን አቆጣጠር እንዲሁም የሀገራችን የኢትዮጲያ ዘመን አቆጣጠር የሚጠቀስ ነው ፡፡ እነዚህ በዋነኝነት በዓለም ሀገራት ይታወቁ እንጂ በአንድ ሀገር ውስጥ እንኳን በርካታ ጎሳዎች የተለያዩ የዘመን አቆጣጠር አላቸው ፡፡ ለምሳሌ በሀገራችን የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምበላላ ፣ የወላይታ ጊፋታ እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው ፡፡ የአራቱም ዘመን አቆጣጠር አመጣጥና ይዘት በተመለከተ በቅንድል ዲጂታል መጽሄት የ2014 ዓ . ም የበዓል ልዩ ዕትም በሀገሬ አምድ ላይ በስፋት ለመዳሰስ ሞክረናል ፡፡ አዲስ አመት በኛ በኢትዮጲያውያን ከአመት በዓልነት የዘለለ ጥልቅና ሰፊ ትርጉም አለው ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጲያ የራሷ የዘመን ቀመር አቆጣጠር ያላት ከመሆኗም በላይ በአለም የራሷን ምስልና ክብር ያኖረች የ13 ወር ጸጋ የታደለች ሀገር ናት ፡፡
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 5