ቅፅ_2_ቁጥር_10 | Page 33

የቤሰብ ወግ

ትንሹ እድሜዋ ግን ማየት ያለባትን ሁሉ ግን አሳያት ። አይኖቿ እስከአለማየት ደርሰው ነበር ፣ እግሮቿ የደረሰባቸው ጉዳቶች ትዳር ሥደት ብቸኝነት ሁሉንም ሆና አየችው ። የተቸገረ ፣ የተራበ ፣ የተጠማ ፣ የታረዘ ፣ አይታ ማለፍ አትችልም :: እጆቿ መሥጠት እሥከቻሉ ድረሥ ትዘረጋለች ። እቤታቸው ውስጥ ትርፍ ነገር አይታሰብም ። ልባሽ ልብሶችን ማናችንም ለሰው ልንሰጥ እንችላለን ። ነገር ግን የአልጋ ልብሥ ከቤት ደብቆ የበረደን ሠው ማልበሥ የማይታመን ደግነት ይመሥላል ልጅት ግን አድርገዋለች ።
ጌታለም የተዘነጋ ፣ አሥታዋሽ ያጣ ፣ ህይወቱን በጎዳና የሚመራ ከህይወት መሥመር ከወጣ ቆየት የሚሉ ክፉ የመከራን ወቅቶች በራሱ ዓለም ሲመራ የቆየ በአእምሮ ህመም የሚሰቃይ ሠው ነው ። እሡንም ሠዎች አይረዱትም ጌታአለምም ማንንም አይረዳም አይቀርብም ። ግና ሳይደግሥ አይጣላምና ጌታ ዓለምን ከወግዲ ሠአዳ ንጋቴን ከሊሞ ከምከም ባህርዳር አምጥቶ አገናኛቸው ። ሠአዳ መክሊቷን ፍለጋ ላይ ናት ግን እንዴት እና መቼ የት እንደሚሆን ግን ፈፅሞ አታውቀውም ።
ይህች በደግነት ሚዛን ላይ እኩል ተደርጋ የተሠራች ወጣቷ ሠአዳ ንጋቴ ከአረብ ሃገር ሥደት ሥትመለሥ በቀጥታ የሔደችው እንጅባራ የሚኖረው ወንድሟ ጋር ነበር ። የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከሥደት ተመላሾችን እራሳቸውን እንዲችሉ በተደረገ ጥረት ውሥጥ ከሥደት ተመላሽ ሥለመሆኗ ያላትን ማሥረጃዎች በመያዝ የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር በአነሥተኛና ጥቃቅን ውሥጥ ቁርሥ ቤት ከፍታ የራሷን ህይወት መምራት ጀመረች ።
ወጣቷ ሠአዳ እንጅባራ ከተማ ዋግ ህምራ አደባባይ ሽሮ ቤት ከፍታ እየሰራች ነው ። ግና የምታየውና የምትሰማው የህሊና እረፍት ነሳት እንጅባራ ከተማ ዋግ ኽምራ አደባባይ ተብሎ በተሰየመው የከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል የለየለት በሚባል ደረጃ ልብሱን የጣለ ፣ የሚመገበውን ከአፈርና ጠጠር ለይቶ የማያውቅ በተቀመጠበት የሚጸዳዳና በላዩ ላይ ያለው ጸጉር በከፍተኛ ሁኔታ ያደገና ተባይ በግልጽ የሚታይበት ጎልማሳ ሁልጊዜም በጸጥታ ይታያል :: ጎልማሳው ከየት እንደ መጣ ወደ አካባቢው መቸ እንደመጣ የሚያውቅ ሰው የለም :: በዚች አደባባይ ላይ ግን ለሰባት ዓመታት አንዳች ነገር ሳይናገር ተቀምጦ መታየቱ የዘወትር ትዕይንት ነው :: ምንም ይሁን ምንም አንዳች ቃል ሲናገር ተሰምቶ አይታወቅም :: ረሃብ ሲጸናበት ቀንም ሆነ ሌሊት በመጮህ እጆቹን ሲነክስ ከታዬ የአዕምሮ ሕመምተኛው ጌታለም መርቻው ርቦታል ማለት ነው ::
ባልጠበቀችውና ባልገመተችው ሠዓት የሠአዳ መክሊት በጌታለም ውድቀት ውስጥ ካልተገለጥኩ እያለ ይታገላት ጀመር ። ነገሩ የታይታ ፍላጎት አልነበረምና ከውሥጥ ፈንቅሎ የሚወጣ ማንነቷ ለማመን የሚከብድ እንዲሁም በሴት ልጅ አቅም ይቻላል የማይባል ትልቅ ገድል ሀ ብላ ጀመረች በድልም ተወጣችው ።
ከዛም ማንም ይሆናል ብሎ ከማይገምተው ጎዳና አንስታ ከራሷ ጋር በዛች ጠባብ ኮንቴነር ውሥጥ በማኖር በፍቅር የተዋበ ደግነቷን አሳየችን ። በእድሜ ገና ብዙ ያልተራመደችው እንሥት ሠአዳ ንጋቴ ። ዛሬ ጌታአለም አዲሥ ሠው አዲሥ ማንነትን ተላብሧል ይህንን የበጎነት ሥራዋን የተመለከቱ ሁሉ አድናቆት ይቸሩዋት ጀመሩ በየማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ መነጋገሪያ ሆነች ።
ሠአዳ ንጋቴ አንዴ የተፈጠረችበት አላማ ለዚህ ነበርና ጌታለምን ከወላጆቹ ጋር ካገናኘችው በኋላ ለዓመታቶች ልብሥ ያልቀየረውን ወጣት ከወደቀበት በማንሳት በሚያሥገርም ፍጥነት የተሻለ ሠው ሆኖ ወደማህበረሠቡ እንዲቀላቀል አስቸጋሪ ግዜዎችን እየታገለች ትገኛለች ። ወጣቷ የበጎ ሰው እንቅልፍ የላትም የተቸገረ የወደቀ አለ በተባለበት ሁሉ ቀድማ ትደርሳለች ። ቤቷን ዘግታ ካገር ሃገር ለሠው ልጆች ፍቅር ለመሥጠት የዘወትር ሥራዋ ነው ። ዘር ቀለም ሐይማኖት አይገድባትም ። ድንበር የለሽ የሰላም ለጋስ የፍቅር የመሥጠት ተጓዥ ናት ።
ሴት ናት በዛ ላይ ወጣት ብዙ ነገሮችን ተቋቁማ እንደወፊቷ ከእጇ ቢያጥራት የአፏን የምታካፍል ለብዙዎቻችን ምሳሌ የምትሆን ወጣት ናት ።
ከላይ መግቢያዬ ላይ የተጠቀምኩት የቢልጌት ታሪክ ። ለዚህች ታዳጊ የበጎነት ፈርጥ ግዜ ሠፍሮ ቀን ቆጥሮ የሚመሠክርላት መምጣቱ አይቀሬ ቢሆንም ። እይታን እና እውቅናን ፈልጋ ሣይሆን የተፈጠረችበት ፅኑ አላማ ነውና ወጣት ሰአዳ ንጋቴ ነገ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሳ እንደምናያት እግርጠኛ ነኝ ። “ የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያሥታውቃልና ! “ አበቃሁ ።
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 33