የቤሰብ ወግ
መምህራን
ጌቱ በቀለ በዳዳ
እንኳን ለአዲሱ ዘመን አደረሳችሁ ውድ የቅንድል ድጅታል መጽሄት አንባቢያን ። ሰላማችሁ ይብዛ ። ለዛሬ ላስነብባችሁ የፈለኩት ስለ መምህራን ነው ። ስለ ጥንታዊ የኢትዮጵያ መምህራን ። ኢትዮጵያን ትውልድ እንዲጠብቃት ታላቁን ዎጋ የከፈሉትን ጥንታውያን የኢትዮጵያ መምህራን ክብር የሚገባቸው ቋሚ ታሪክ ያላቸው የኢትዮጵያና ትውልዷ ባለውለታ ናቸው ። በህይወት ላሉት ሽልማት ላለፉት ደግሞ መታሰቢያ ሐውልት ሊቆምላቸው ፤ የመታሰቢያ ቀን ከአመቱ ቀናት ውስጥ ተመርጦ ሊከበርላቸው ይገባል ።
ትናንታችንን ዞር ብለን ካስተዋልን እነዚህ ሊቃውንት ሁሉ ለሀገራችን ታላላቅ ስራን የሰሩ እውቀትን በነጻ ያካፈሉ ፤ በኢትዮጵያ ታላቅ ዝናን ያተረፉ ናቸው ። ይኽን ሁሉ ሞያና የሀገር ባህል የጠበቁና ያስተላለፉ ፤ ሕዝባችንን ስልጣኔን ይዞ እንዲቆይ በቀላሉም ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ የቻሉ እነርሱ ባስተማሩት ትምህርት ነው ።
ህዝቡን ህዝብ አድርገው ሐሞተ ቆራጥና ደፋር አድርገው ለነጻነትና ለሃይማኖቱ ተጋዳይ እንዲሆን የሰሩና ያስተማሩ እነርሱ ናቸው ።
ሀገሩን አፍቃሪ መንግስታቸውን አክባሪ በጠቅላላው የያዘውን ሁሉ ጥቅሙንና ጉዳቱን አውቆ ኢንዲኖርና መመሪያ የሰጡ እነርሱ ነበሩ ። ይሄን ሁሉ ለማድረግ የቻሉት ግን የኢትዮጵያ መምህራን መከራ የማያሸንፋቸው ፤ ማግኘትና ማጣት ቢፈራረቅባቸውም ግምት የማይሰጡት ፤ በረሃብ የማይፈቱ ፤ ማዕረጋቸውን እንጅ ሆዳቸውን የማይወዱ አባቶች ስለነበሩ ነው ። አባቶቻችን ትልቅ እውቀት የነበራቸው ናቸው ። ስለዚህ በባህረ ሀሳብ በቀላሉ የሚዋኙ ለጥበብ በቃኝ የማይሉ ነበሩ ። ሞያችን እና ስልጣኔያችን እንዳይጠፋ በማለት ተርበው ከመማራቸው ይልቅ ተርበው ማስተማራቸው በሰፊው ይነገርላቸዋል ።, በማግኘታቸውም ሆነ በማጣታቸው ቸል ሳይሉ እውቀት ሲዘሩ ሀገራቸውን ከአፍሪካ ለይተው የእውቀት ምንጭ የነጻነት መዝገብ አድርገው መቆየታቸው የታወቀ ነው ።
ዛሬን ከሃሳብ ፌርማታ አረፍ ብሎ ስለ ጥንታዊ የኢትዮጵያ መምህራን የሊቃውንትነታቸውን የእውቀት ጥልቀት ፤ በእነርሱ ዘመን ስለሰሩት ባህላችን ዞር ብሎ የሚመረምር ባለመኖሩ ታላቁን ውለታቸውን ግምት ሊሰጥ የቻለ የለም ። ጥንታዊ እውቀታቸውም ከቀን ወደ ቀን እየኮሰሰና እየተዋረደ ይገኛል ። በጥንት ዘመን የሆነ እንደሆነ መምህራን በአንድ አይነት እውቀት ሳይወሰኑ የጠፋውን በመፈለግ የደከመውን በማጽናት ከእውቀት ወደ እውቀት ይራመዱ ነበር ። አንድ መምህር ከሁለትና ሶስት አይነት እውቀት በላይ ስለአለው ያን እውቀቱን በህይወት ሳለ ለማካፈል ሲል ልእይወቱ ሳይሳሳ ለተማሪው በሚመቸው ሀገር እየዞረ እየተንከራተተ ያስተምር ነበር ። ለማስተማርም አሁን በኋላ ነገ በማለት ጊዜ ሳይወስን በቀን በሌት ያለ ግዜ ገደብ ያስተምር ነበር ። ለዚህ ሁሉ ድካሙ ተመጣጣኝ ክፍያን የሚከፍለው አልነበረውም ። ህዝቡኳ ቢቀጥረው እርሻ ቢያርስለት ከአዝመራው ጥቂት ለእለት ጉርሱ ቢሰጠው እንጅ ለኑሮውና ትዳር ላላቸውም በቂ ወረትን አይቋጠርለትም ነበር ።
መምህሩ ሁሉንም የችግር ግትልትሎሽ ሳያስበው በማስተማሩ ብቻ እየተደሰተ መንፈሱ ጸንቶ ችግሩን አሸንፎ ይኖራል ። ቤት ውስጥም የሚገጥመውን የወቀሳ ፈተና ከቁብም ሳይቆጥር ትውልድን በመተካቱ ትጋቱ ይበረታበታል ። አንዳንዴ ያለእረፍት ሌተ ቀን በማስተማር በማሳለፉ ለትዳሩ የሚሆን ወረትን ባለማምጣቱ እራት በሚጠይቅበት ግዜ ሚስቱ ተናዳበት ከመሶቡ ድጓን ከድና አቅርባለታለችም ይባላል ።
ጥንታዊ መምህራን የሚገጥማቸው ፈተና ተነግሮ አያልቅም ። ሲያስተምሩ በመቆየታቸው የሚጎዱ በበሽታ ተሰነካክለው የእድሜ ልክ በሽታን የሚያተርፉ ሲሰቃዩ የሚኖሩና ብዙ ማገልገል እየቻሉ ባጭሩ በሞት የሚለዩን ስፍር ቁጥር የላቸውም ነበር ። ይሄን ሁሉበየዘመኑ ዎጋ እየከፈሉ ሀገርን ለማስቀጥል ሀገር በቀል እውቀትን ለማስፋፋት የዋሉትን ውለታ ከቁም ነገር ያልቆጠረው የመጣው ስርዓት በኮረጃቸው የትምህርት ፖሊሲዎቹ ውስጥ ለነሱ የማስተማር ጥግን ባለመተው በሃገርና ትውልድ ላይ የበዙ ውጥንቅጦች እንዲፈጠሩ ክፍተቶች ተፈጥሮአል ።
ኢትዮጵያ በትምህርት የረዥም ግዜ ታሪክ እንዳላትና በ4ኛው መቶ ክዘመንመንፈሳዊ ስለመጀመሩ ታሪክ ይናገራል ። በሁለቱ ትላልቅ ሃይማኖቶች ውስጥ ባሉ ጥንታዊ መምህራን ለህዝቡ ጠቃሚ የሆኑ ባህላዊ አልባሳትና ቁሳቁስ ስርዓት ስነ ቃላዊ እሴቶችን አውርሰውናል
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 34