ጥበባት
የቴዲ አፍሮና የጂጂ ኢትዮጵያና አደዋ በወፍ በረር
ጉቺ ሽመልስ
(( ይህ ፅሁፍ ጭብጣዊ ቅኝት እንጂ ማወዳደር የማይዳዳዉ አጭር ዳሰሳ ነዉ ።))
ጥበባዊ ስራዎች ባላቸዉ ዋጋ ከመዳኘት ይልቅ ቲፎዞአዊ ዝንባሌ ባላቸዉ ተደራሲያን ዋልታ ረገጥ ቡራኬ እና እርግማን ማስተናገድ እጣ ፈንታቸዉ ሆኗል ። የማወዳደር ልክፍት ተጣብቶናል ።
‘ ከአዳም ረታ እና አለማየሁ ገላጋይ ?’ ‘ ከኤፍሬም ስዩምና በዕዉቀቱ ስዩም ማን ይበልጣል ?’ ‘ ጂጂ ወይስ ቴዲ ?’ ማብቂያ የለዉም ።
ዘመነኛ ስራዎች በሂሳዊ ትንታኔ የመታየት እድል ተነፍገዋል ። ከያንያን ባበጁት ግላዊ ፍኖት የሚጓዙ እንደመሆኑ መጠን በራስ አራዳድና ምናብ ጉዳዩን ሊገልፁ ይችላሉ ። በዚህ ሁኔታ ማበላለጥ ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ይሆናል ። በእርግጥ ስራዉ በሚኖረዉ ፍሬ ነገር እና በአድማጩ ግላዊ ብያኔ በር መጠርቀም የማይቻል በመሆኑ ሁሉም በጣዕም ልኬቱ አንዱን ማስበለጥ ተፈቅዶለታል ። በእኔ በኩል ግን ታካች ንትርክን ለመክላት ቢበጅ በሚል ይህ ንፃሬአዊ አተያይ እዉን ሆነ ። እነሆ ...
ፈር መያዣ
ሀገር ንድፉ ልቦና ላይ ነው ። ‘’ ሀገር ሰው ነው ’’ የለም ‘’ ጋራው ሸንተረሩ ወንዙ ነው ’’ አይነት ጉንጭ አልፋ ክርክር ውስጥ አንገባም ። አይሁዶች ለ1900 ዓመት ሀገር አልነበራቸው ። አርታርቲካ እና ሌሎች ሰው አልቦ በመሆናቸው ሀገር አይባሉም ። ባለቅኔው አያሙሌስ ፦
‘’ የጤናዬን ነገር አደራ የዘፍጥረቱንም ጭምር ብቻዬን ችዬ አልቆምም ያለ ፅንፈ አለሙ ድምር ’’ አይደል የሚለው ?
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 22