ነዋል አቡበከር newalabubeker13 @ gmail . com
አጃዒብ
ምኞት ያሰከረው የሰው ልጆች የዘመን መለወጫ
ዘመን ከዘመን ሲለወጥ ፤ የዘመን መቁጠሪያዎችቻችን ወደፊት ሲራመዱ ፤ አዲስ አመት ሲጠባ ፤ አደይ ሲፈነዳ ፤ ምድርን ተስፋ ሲሞላት እኛም “ እሰይ አዲስ አመት እንቁጣጣሽ እንኳን ደህና መጣሽልን ” ብለን መቀበል ፤ ከመፈቃቀሩም ከመጠያየቅ መዘያየሩንም ሁሉ ያውቅበታል ሀበሻ ። ታዲያ ከነዚህ ጋር ሁሉ አብሮ የሚሄደው ጥልቅ የመለካም ዕድል ምኞት መብዛት አስገረመኝና ለመሆኑ ሌላው አለምስ አዲስ አመትን እንዴት ያከብር ይሆን ስል የ Google ን ቋት በረበርኩኝ ። ያገኘኋቸው መረጃዎች ግን አጃኢብ የሚያሰኙ ሆነው አገኘዋችወ ። ለካስ ባለፉት ነገሮች የተማረረው የሰው ልጅ በአዲሱ አመት መልካም እድል እንዲገጥመው የማያደርገው ድርጊት ፤ የማይከውነው ነገር የለም ።
የምተርክላቹ በእንግዳ ባህልና ልምዳቸው አለምን ስለሚያስገርሙት የኬንያ አርብቶ አደሮች ወይም የሀመር ሰዎች አልያም የአማዞን የጫቃ ነዋሪዎች አይደለም ። የማወራቹ አጉል ልምድና ባህልን ፤ ምክንያት አልባ ድርጊትና እምነትን አልፈናል ስለሚሉትና ስለሚንቁት የምዕራባውያን ሀገራት አዲስ አመታቸውን መልካም ለማድረግ የሚከውኑት አሰገራሚ አንዳንዴም አስቂኝ ልምድ ነው ።
ለምን ከአየር ላንድ አንጀምርም ። እንደው አንዳንድ ግዜ ህይወት ምርርር አድርጋቹ ፤ መኖር አንገሽግሿቹ “ ኧረ የት ሂጄ ኡኡኡኡ ልበል ?” ብላቹ አታውቁም ? “ እንደው መንግስት ግን ምን አለ የመረረው ሁሉ እየሄደ “ ኡኡኡኡ ” ብሎ ያለ ሀፍረት የሚተነፍሱበት ተቋም ቢያቋቁም ። አሁን እንባን ከመጠበቅ ይሄ አይቀልም ?” ብለው ተመኝተው አያውቁም ? የኛ ይቆየን ። አየርላንዳውያን ግን ለዚህ ፍቱን መፍትሄ አዘጋጅተዋል ። በእነሱ የአዲስ አመት ወቅት የተለመደ አንድ ልምድ አለ ። ዳቦ ደጃፋቸው ላይ ማንጠልጠል ።” መጥፎ መንፈስን አሽቀንጥሮ የበዛ ፀጋን ይስባል “ ብለው ያምናሉ ። ታዲያ የዳቦው መጥፍ መንፈስን የማስወጣት ስራ የሚሰራው እስከ ደጃፍ ድረስ ብቻ ነው ። ከዚያ በኋላ ፍፁም እንዲጠፋ የሚከወን አንድ ድርጊት አለ ። ከቤት የወጣው ክፉ መንፈስ ፈቀቅ ብሎ ከደጃፍ እንዳይጠብቃቸው በእኩለ ለሊት ድቅድቅ ጨለማ ወደ በራፋቸው ይወጡና “ ኡኡኡኡኡኡኡ ” ብለው በጩኸት ያቀልጡታል ። ህፃን አዋቂው ፤ አዛውንት ወጣቱ የሚችለውን ያህል ሁሉ ይጮሀል ። በጩኸቱ የድሮውን አባሮ “ አዲስ አመት ሆይ በል
አሁን ግባ ” ሊሉ ። ደግሞ ይኼኛው አርጅቶ ጮኸው እንዳስገቡት ጮኸው እስኪያወጡት ።
አስተውሉ እንግዲ አየርላንዳዊያን አዲስ ዘመንን አስታከው አገር ምድሩን በጩኸት ሲያቀልጡት የዴንማርክ ሰዎች ደግሞ አዲስ አመትና የቤት እቃ መስበር የኛ እንቁጣጣሽና አበባይሆሽ እንደማለት ነው ። አይነጣጠሉም ። ልክ የኛ ታዳጊዎች አዲስ አመት ሲደርስ ስዕል ስለው አልያው ካርድ አዘጋጅተው ስጦታ እንደሚሰጡት ዴንማርካውያንም በአዲስ አመት የፍቅር መግለጫ ድርጊታቸው የቤት እቃዎቻቸውን አውጥተው የወዳጆቻቸው ቤት ላይ እንደ ናዳ መሰባበር ነው ። ብርጭቆ አይቀር ሸክላ ፤ ማንኪያ አይቀር ሹኪያ ከማዕድ ቤት እየተጓዘ ሊያውም በእኩለ ለሊት ይወረወራል ይሰበራል ። “ ታዲያ የሚወረወርበት ሰው ምንም አይልም ?” ብለው ግራ እንዳዳይገባዎት ። የዴን ማርክ አባወራ የወዳጆቹን ብዛትና የፍቅራቸውን መጠን የሚለካው ከደጃፉ በተከመሩ የእቃ ስብርባሪዎች ነው ። ለሊቱ በብርጭቆ ስባሪ ካልተናወጠ ፤ ጣሪያው ካልተንጋጋ አውዳመቱ አይደምቅም አይሞቅም ።
መቼም በበዐል ወዳጅ ዘመድን መጠየቅ የበዐሉ ድምቀት መሆኑ ጥርጥር የለውም ።” ተሰብስበው ካልበሉ ፣ ካልተጓራረሱ ፣ ካልተገባበዙ ምኑን በዐል ሆነ “ ይሉ የለ ደጋግ እናቶቻችን ። ነገር ግን በዐሉ የሚከበረው ከሙታን ጋር ወይም ከእንሳስ ጋር ሲሆንስ ? አዎ ቺሊያውያን የዘመን መለወጫን የሚያከብሩት ከሙታን ወገኖቻቸው ጓን እያወጉና እየተጨዋወቱ ነው ። ሮማንያን በበኩላቸው አዲስ አመት የቤት እንስሳዎቻቸውን ማዕድ ጋብዘው በቋንቋቸው ሊያወጓቸው እየጣሩ በአሉን በደስታ ያሳልፋሉ ። በበሬውን ወይም በጉን ፣፤ ዶሮውን አልያም ፈረሱን ከመዐዱ ጋብዘው “ ብሉ በሞቴ ... ያዙ እንጂ ... ከምን ልጨምር ” እየተባባሉ መሆኑ ነው ። ለምን ቢባል ? መልካም እድልን ፍለጋ ነው ። ይህ ድርጊት መልካም ፀጋን እንደሚያመጣ ስለሚያምኑ ።
የመልካም ነገር ናፍቆት ሪስያውያንም ብዙ ያደርጋል ። በሩስያ የአዲስ አመት ዋዜማ የሚከወን አንድ የታወቀ ልማድ አለ ። ታዲያ ችቦ ማንደድ አይደለም ። እንዲህ ነው ነገሩ ። የአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት ላይ ሩሲያውያን በያሉበት ሆነው በቀጣዩ አመት እንዲሆንላቸው የሚፈልጉትን ነገር በወረቀት ይዘረዝራሉ ። ዘርዝረውም አያበቁም ያቃጥሉታል ።
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 16