በሀገራችን ዝናን ለመልካም ስራ መጠቀም ክብርና እውቅናን ጠብቆ ለወጣች አርአያ መሆን እንደ ስያሜውም አርቲስት የህዝብ ልጅ የሚለውን የሚመጥኑ ጥቂቶች ናቸው ፡፡ አርቲስት የህዝብ ልጅ ሚሆነው እውቅናውን ፣ ክብሩንና ማንነቱን ለሰጠው ህዝብ መልሶ በቅንነትና በምክንያታዊነት ማገልገል ሲችል ነው ፡፡ በተለይም እንስት አርቲስቶቻችን ብዙ ተከታይ እንዳላቸው መጠን ምሳሌ የሚሆን ስራን ሲሰሩ መመለከት ከፍ ያለ ምስጋናና ክብር ሊያሠጣቸው ይገባል ፡፡ በጉዲፈቻ ፊልም አድናቆትን አግኝታ በርካታ የመድረክና የፊልም ስራዎችን አቅርባለች ፡፡ በተለይም በገመና ድራማ ላይ በነበራት ድንቅ ስራ ብዙዎች ልብ ውስጥ መግባት የቻለች ልባም ተዋናይ ናት ፡፡ ዝነኝነትን ለመልካም ስራ ከማዋል በዘለለ በስነ ምግባርና በህይወት እንቅስቃሴዋ ለብዙ ሴት አርቲስቶችና ወጣቶች ምሳሌ ያረጋታል ፡ ፡ በልብ ህመም ለሚሰቃዩ ወገኖች ከፊት ሆና በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እየከወነች ነው ፡፡ ልባም ሆና በልብ ህመም የሚሰቃዩ ህጻናትን ተስፋ እየመገበችና ድጋፍ እያሰባሰበች ብዙ ስራ ሰርታለች ፡፡ አሷ በጎ አድራጎት ሲባል ቀዳሚ ፣ ቅንነት ሲባል ምልክት ፣ ክብርን ጠብቆ ምሳሌ መሆን ለሷ የሚገቡ መግለጫዎች ናቸው ፡፡ አርቲስት መሰረት መብራቴ ብዙዎችን ወደ ኪነ-ጥበብ እንዲገቡ ሰርቶ መቻልን ያሳየችና ዝናን ክብርን ጠብቆ ማቆየትን ያወረሰች የቅኖች ምሳሌ ብለን በዛሬው ዕትማችን ልናመሰግናት ወደናል ፡፡ መሰረት በቀጣይ በበርካታ ስራዎች መብራት እንደምትሆን እንተማመናለን ፤ ጤናና እድሜ ተመኘን ፡፡
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 14