ቅፅ_2_ቁጥር_10 | Page 20

አዕምሮ ጤና

ፍራኦል መስፍን firaolmesfin8 @ gmail . com

የማይታይ ቁስል

የህይወት ገጠመኝ የሌለው ሰው ይኖር ይሆን ? ይብዛም ይነሰም ሁላችንም ዛሬ እስካለንበት ድረስ ለመልካም ነገር ወይም ደግሞ ለመጥፎ ነገር ተጋልጠናል ። ብዙ ሰዎች እጅግ አስደንጋጭ ነገር በራሳቸው አልያም በቤተሰቦቻቸው ላይ ገጥሟቸው ተጨንቀው ፣ ተረብሸው ኑሮን በመከራ ይኖራሉ ። በአደጋ ( ተሽከርካሪ )፣ በወንጀል ( በድብደባ ፣ ስለት መወጋት )፣ በጦርነት ፣ ጾታዊ ትንኮሳ ፣ ተፈጥሮዊ አደጋ ( ጎርፍ ፣ እሳት ፣ መሬት መንቀጥቀጥ ) ወዘተ በኋላ የሚፈጠር የአዕምሮ ህመም ድህረ ሰቀቀን ጭንቀት ( Post-Traumatic Stress Disorder ) በመባል ይታወቃል ። ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት ( ፒቲ ኤስ ዲ ) በቀድሞዎቹ ዓመታት የሚታወቀው ሼል ሾክ ( የጦር ሜዳ ጭንቀት ) በሚል ስያሜ ሲሆን ስለ በሽታው ይደረጉ የነበሩት ጥናቶች በዋነኛነት ያተኩሩ የነበረው ከዘመቻ በተመለሱ ወታደሮች ላይ ነበር ። ዛሬ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል ። ወታደር ባትሆንም እንኳ ፒ ቲ ኤስ ዲ ሊያጋጥምህ ይችላል ። የሆነ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ ከደረሰብህ ለእንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት ልትጋለጥ ትችላለህ ። ሁኔታው የጦር ሜዳ ውሎ ወይም የግዳጅ ወሲብ ለመፈጸም የሚደረግ ሙከራ አለበለዚያም የመኪና አደጋ ሊሆን ይችላል ። ብቻ ይህ ሁኔታ ከተፈፀመብን ፣ ወይም ሲፈፀም በስፍራው ከነበርን አልያም ከሰማን የዚህ ጭንቀት ሰለባ የመሆን እድላችን ሰፊ ነዉ ።
ሆኖም ሁሉም አሰቃቂ ሁኔታዎችን ያሳለፈ ሰዉ ሁሉ ከአሰቃቂ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት ( PTSD ) ያጋጥመዋል ማለት አይደለም ። ነገር ግን በርካታ አሰቃቂ ሁኔታዎች ሲፈራረቁ ሰዎችን ይበልጥ አደጋ ላይ እንደሚጥሉ እናውቃለን ። ድንገተኛ የሆነ አስደንጋጭ ሁኔታ በሚያጋጥምበት ጊዜ ሰውነት አንዳንድ ሆርሞኖችን በከፍተኛ መጠን በማመንጨት እነዚህ ሆርሞኖች የስሜት ሕዋሳት ለአደጋ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ያደርጋል ። እንደ ወትሮው ቢሆን የሆርሞኖቹ መጠን አደጋው ካለፈ በኋላ ወደ ቀድሞ መጠናቸው ይመለሳሉ ። በፒ ቲ ኤስ ዲ ሕሙማን ላይ ግን ከፍ እንዳሉ ይቆያሉ ።
አሰቃቂ ሁኔታ አጋጥሞህ ከነበረና ሁኔታው ተመሳሳይ ችግር ጥሎብህ የሄደ ከሆነ ይህ የደረሰው ባንተ ላይ ብቻ አለመሆኑን መገንዘብህ በጣም አስፈላጊ ነው ። ፒ ቲ ኤስ ዲ ማንም ሰው ሊያጋጥመው የሚችል ቀውስ ነው ። ከስርጭት አንፃር PTSD ሴቶች ለይ ይበዛል ። 10 በመቶ ለሴቶች ( ጾታዊ ጥቃት ስለሚበዛ ) ፣ 4 በመቶ ለወዶች ( ከግጭት ጋር በተያያዘ ) እንዲሁም ወታደሮች ለይ 30 በመቶ እንደሚጠጋ ጥናቶች ያሳያሉ ። ወጣቶች ላይ ደግሞ ስርጭቱ እጅግ ከፍተኛ ነው ።
ማንም ሰው ከዚህ ችግር የተጠበቀ አይደለም ። ነገር ግን ማህበራዊ ተሳትፏቸው አነስተኛ የሆኑ ሰዎች የበለጠ ሊጠቁ ይችላሉ ፤ እንደ ምሳሌ ብቸኛ ሰዎች ፣ ትዳር የሌላቸው ( በሞት አልያም በፍች ሊሆን ይችላል ) ፣ ከፍተኛ ድህነት ዉስጥ ያሉ ( የወንጀል ሰለባ ሰለሚሆኑ )፣ አብዝቶ የሱስ ተጠቃሚዎች ፣ አንዳንድ የስብእና ችግር አይነቶች ፣ ተያያዥ ጭንቀቶች እንዲሁም ድባቴ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው ።
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 20