ሳይ-ቴክ
ለዓለም ከንፈ
ፎቶግራፈር በማርስ ላይ ?
ማርስ ላይ ፎቶግራፈር ? ከመሬት በ2020 እ . ኤ . አ ተልካ በፌብሩዋሪ 2021 የማርስ ምድር ላይ ካረፈችበት ጊዜ ጀምሮ የናሳዋ ፐርሰርቬራንስ ሮቨር ( የአማርኛ አቻዊ ትርጉሟ አይገበሬ የሚለውን ቃል ሲይዝ ) እስከ ዛሬ ድረስ ወደ ናሳ ጄት ፕሮፖልሽን ላቦራቶሪ ( JPL ) አስገራሚ እና አነጋጋሪ ምሥሎችን በተገጠሙላት ዘመናዊ ካሜራዎች አማካኝነት እየላከች ትገኛለች ። ዛሬ በሳይ-ቴክ አምዳችን ፐርሰርቬረንስ ምን እንደሆነች ፣ ለምን ወደ ማርስ ዓለም እንደተላከች ፣ እዛም ሄዳ ምን እንደምትሠራ እና ለሰው ልጆች የወደፊት የማርስ ተልዕኮ ምን ፋይዳ እንደምትጫወት እናያለን ።
ፐርሰርቬራንስ ሮቨር ምንድን ናት ? ፐርሰርቬረንስ ናሳ ከዚህ ቀደም እንደላካቸው ሮቨሮች ( ለምሳሌ ኪሪዮሲቲ ) ሮቨሮች ማርስን ለማሰስ በ2020 ዓ . ም ከምድረ አሜሪካ የመጠቀች ሮቨር ናት ። ሮቨሮች በሰው ልጆች ተገጣጥመው በሌላ ዓለማት ፣ ጨረዋዎች ላይ እዛው የዓለማቱ ምድር ላይ በመሄድ መረጃን የሚሰበስቡ ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ታግዘው ስራቸውን በራሳቸው የሚሰሩ የሮቦት መኪናዎች ናቸው ። እንደው ለቃሉ አጠራር ነው እንጂ ውድ የህዋ መኪናዎች ናቸው ማለትም እንችላለን ። እነዚህ ሮቨሮች ከመሬር ላይ ካለ የቁጥጥር ጣቢያ ጋር በመገናኘት አልፎ አልፎ አስፈላጊ መረጃዎችን እና ትዕዛዞችን ይቀበላሉ ብሎም የሰበሰቡትን መረጃ መልሰው ይልካሉ ። ፐርሰርቬረንስም ተመሣሣይ ስራዎችን ማርስ ላይ ለመስራት ነው እንግዲህ በናሳው JPL ቁጥጥር አማካኝነት ቀድማ በ2020 መባቻ የተላከችው ።
ለምን ማርስ ? እንደሚታወቀው ፣ ከዚህ በፊት እንደተሰሩት ጥናቶችም ፤ ለመሬት ተቀራራቢ በሚባል መልኩ የሰው ልጆች አሁን ባለው የቴክኖሎጂ አቅማቸው ሄደው ለማጥናትም ሆነ ከተቻለ ለመኖር ካለንበት የፀሐይ ስርዓት ውስጥ ብቸናዋ አመቺ የሆነችው ዓለም ማርስ ብቻ ናት ። ይህም የሆነው ከስምንቱ ዓለማት ሁለቱ ( ሜርኩሪ እና ቬነስ ) ከፀሐይ ጋር ባላቸው ቅርበት ምክኒያት ከፍተኛ ሙቀትን በመያዛቸው ፤ ዐራቱ የተቀሩት ዓለማት ( ጁፒተር ፣ ሳተርን ፣ ኔፕቱን እና ዩራኑስ ) ከጋዝ የተሰሩ በመሆናቸው ለመሬት ትንሽም እንኳን ቀረቤታ ያላት ዓለም ማርስ በመሆኗ ፤ መሬት ላይ ያሉ ታዋቂ የህዋ ሳይንሥ አጥኚዎች ማርስን ለማጥናት መርጠዋል ። ከቢሊዮን ዓመታት በፊት ማርስ ልክ እንደ መሬት ውቅያኖስ እና ህይወት ሳይኖርባት እንደማይቀር እና የውስጣዊ ሙቀቷ በመቀነሱ ምክኒያት ከባቢ አየሯን ማጣቷና ውቅያኖሶቿ ሟሸው እንደጠፉ የሚያሳዩ ጥናቶችን ተመልክተናል ። ይህንን ምክኒያት በማድረግ ናሳ ፐርሰርቬረንስን እዛው ማርስ ላይ ሄዳ መረጃዎችን እንድትሰበስብ ልኳታል ።
ማርስ ላይ ከሄደች በኋላ ምን ትሠራለች ? ማርስ ላይ ከዚህ በፊት ህይወት ይኖርበታል የለባሉ ቦታዎች ቀድመው በተላኩት ሮቨሮች አማካኝነት ተለይተው ነበር ። ከእነዚህ ቦታዎች አንዱ ማርስ ላይ ያለው ጂዜሮ የተባለው ቦታ ነው ። ከታች በምስሉ ላይ እንደምትመለከቱት ይህ ቦታ በጥንት ጊዜ ወንዝ ይፈስበት የነበረበት እና ወደ ብዙ ገባሮች ተከፋፍሎ የሚጠፋበት ቦታ እንደሆነ መላ ምት ይቀመጣል ። ይህ የወንዝ መጨረሻ የነበረ ቦታ ለም አፈርን እና ለህይወት ምቹ የነበሩ ማዕድናትን ይይዛል ተብሎ ስለታመነበት አሁን ፐርሰርቬረንስ በዛ ቦታ ላይ ህይወት ስለመኖሩ ብሎም ኖሮ እንደሚያውቅ ለማጥናት ጥልቅ ጉድጓዶችን በመቆፈር ናሙናዎችን ትወስዳለች ። እነዚህን ናሙናዎች በቀጣይ ጊዜ በሚኖሩ ተልዕኮዎች አማካኝነት ወደ መሬት በማምጣት ጥልቅ የሆኑ ጥናቶች ይደረግባቸዋል ። በተጨማሪም ፤ ፐርሰርቬረንስ የሰው ልጆች በቀጣይ ወደ ማርስ ለመጓዝ እና ለመኖር እንዲያስችላቸው የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ ሙከራዎችን ታካሂዳለች ። ከእነዚህም አንዱ ኦክስጅንን ከማርስ ከባቢ እንዴት ማምረት እንደሚቻል በተግባር በተገጠሙላት ቃኚዎች እና ላቦራቶሪ እማካኝነት መሞከር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ተጨማሪ የውሃ ክምችትን ማሰስ ነው ።
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 29