ቅፅ_2_ቁጥር_10 | Page 26

ትዝብት

ሀገራችን ልታድግ የምትችለው

ሌሊቷ ቀን ሲሆንላት ብቻ ነው !

የምሽቱ ፀጥታም ይገርመኛል ። ይሄ ሁሉ ሕዝብ የዚችን ፀሐይ አወራረድ ሳያይ በየቤቱ ሲገባ ቅር አይለውምን ? እላለሁ ። በየቤታቸውስ ምን ይሰራሉ ? እላለሁ ። የሚሰሩትን አስቤ ከጥቂት ነገሮች የበለጠ መዘርዘር አልችልም ” ይላል የግራጫ ቃጭሎቹ ተወዳጁ መዝገቡ ዱባለ ።
ትዝ ሲለኝ ሌሊት ‘ ዎክ ’ የማድረግ ልምድ አላዳበርኩም ። የሌሊቱን ቁር ቀምሼም አላውቅም ። ታድያ ለምን ወጥቼ አላየውም ? የሚል ሀሳብ ሰቅዞ ሲይዘኝ ስምንት ሰዓት ሊሆን ሲል ከቤት ወጣሁ ። የግቢያችንን መዝጊያ እንደከፈትኩ የመንገዱ መብራት ዐይኔን አጥበረበረኝ ( በዚህ ሰዓት መብራቱን የሚጠቀመው ሳይኖር ለምን በራ ? ቀን ከሚያጠፉብን ሰው የማይጠቀምበትን ሰዓት አውቀው አጥፍተው ኃይል ቢቀንሱስ ? የሚል ሀሳብ በዐይኔ በኩል ገባ መሰል )። ዐይኖቼን አሻሽቼ ከዳጃችን ጀምሮ ቁልቁል የተዘረጋውን ኮብል ስቶን ተመለከትኩ ፣ ተኝቷል ። ዛፎቹም እስኪነጋ ድረስ አልቦ እንቅስቃሴ ሆነዋል ።
ኮብሉን ይዤ ወደዋናው አስፓልት አዘገምኩ ። ከርቀት አንድ መኪና እያጓራ ወደ ’ ኔ አቅጣጫ ይመጣል ። መኪናው በቀረበኝ ቁጥር ISUZU መሆኑንና ጫት ወደሌላ ከተማ እያደረሰ እንደሆነ ከልምዴ አወቅሁ ። ተገረምኩ ። አስፓልቱ ላይ ያለፈው አንድ መኪና ብቻ ነው ። ይሄ ማለት አንድ ገጠር ውስጥ ምናልባት በቀን ሊታይ የሚል መኪና ነው ። በዚህ ሌሊት በቋሚነት ሥራችን ብለው የሚሰሩት አካላት ትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ አካላት ጋር ጥበቃ የሚሰሩ ሰራተኞች ናቸው ( ፖሊስ ፣ ዘበኛ )። ( የሌሊቱን ጊዜ ተጨማሪ ክፍያ እየተከፈላቸው የሚሰሩትን ልብ ይሏል )።
ኢትዮጵያ ውስጥ መምሸት ማለት ለአብዛኛው ሰው ከሥራ መፋታት ማለት ነው ለካ ። በቀን ውሏችን ሳንሰራ የምናሳልፈው ጊዜ ለካ ሌሊታችንን እያራዘምንበት ነው ? ለአስራ ስድስት ሰዓት ከሥራ ተፋትተን ( ስምንቱንም ሳንሰራበት ቦጫጭቀነው ) እንዴት እናድጋለን ብለን እናስባለን ? እንቅልፍ እንቢ ሲል እንኳን ወጥተን የምንሰራበት ፣ በሰዓት ጥቂት ክፍያ የሚከፍል ፋብሪካ ለምሳሌ የዱቄት ፣ የካልሲ ፣ የመሳሰሉት ነገሮች ቢኖር ብዬ ተመኘሁ ። ግን ሳስተውለው እኛ ኢትዮጵያውያን አንደኛ ሀገራችን ውስጥ ሲሆን ሥራ ትልቅ እና ትንሽ ብለን እንፈርጃለን ፣ የክብር ጉዳይ ( ውጪ እኮ ቢሆን ዝቅተኛውን እንደምንሰራ ይታወቃል ) ሁለተኛ ሌላው የሰራው ሥራ አይጥመንም ። ከልብስ ፣ ጫማ አቅም ጀምሮ እስከትናንሽ ምርቶች ድረስ ‘ ብራንድ ’ የምናማርጥ ፤ ከሀገር ውስጡ ይልቅ የውጪው የሚያነሆልለን ነን ። ታድያ እኛ ያልተጠቀምነውን ማን ይጠቀመዋል ? እኛስ ካልተጠቀምነው እንዴት እየተሻሻለ የሚሄድ ጥራት ያለው ምርት ይኖረናል ? ታድያ እንዴት ይታደግ ይሆን ? ገጠሮቻችን ‘ ቀን ’ የሚወጣላቸው ቀን መቼ ይሆን ? የአንድ መኪና ድምጽ ከመስማት የሚያድጉበት … መብራት ፣ ንፁህ ውኃ እና የመሳሰሉት መሠረታዊ ነገሮች የሚሟላላቸው መቼ ይሆን ?
ሌላው በሌሊት ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለው እድለኛ ሰው የኪነጥበብ ሰው ነው ። ምክንያቱም ሌሊት በራሱ ዉበት ነዋ ! ቀን ሲሆን ከፀሐይ ጋር ብቻውን የሚያሳልፈው ሰማይ አኩኩሉ የሚጫወቱትን ጨረቃ እና ደመና .. የእነሱን ድብብቆሽ በታዛቢነት የሚመለከቱ እልፍ ከዋክብትን ስለሚያገኝ ብቸኝነቱን ይረሳል ። ወደቤቴ ስመለስ ሰፈሩ ጭር ማለቱ አስደሰተኝ ። ደራሲዎች ይህን ዝምታ እንዴት ይወዱት ይሆን ? ቀን ቢሆን እኮ የህፃናቱ ቡረቃ ፣ የድምጽ ብክለቱ ፣ የአዋቂዎች ትርምስ ሰፈሩን የብድ ቤት ያስመስለው ነበር ። ‘ ከኳኳታው ተነጥለን- ዝም ብለን አብረን ዝም ለማለት ’ እንደሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ቆቃ ድረስ መውረድ አያስፈልግም ። ሌሊት በራሱ ቆቃ ነው ። መምሸቱን ደራሲዎች ፣ ጥበቃዎች ፣ ሾፌሮች እና ሌሎች በሌሊት የሚሰሩት የሚጠቀሙበት ከሆነ ሌላው ማኅበረሰብስ ምን ይሰራበት ይሆን ? የግራጫ ቃጭሎቹ መዝገቡ ዱባለ እንዲህ ይለናል ።
የሚሰሩትን አስቤ ከጥቂት ነገሮች የበለጠ መዘርዘር አልቻልኩም ። ይሔ ሁሉ ሕዝብ እነዚህን ትንሽ ትንሽ የመሰሉ
ነገሮችን ይሠራል ….. ራት ይበላሉ ( ካልበሉ ስለሚራቡ ) ይጠጣሉ ( ካልጠጡ ስለሚደርቁ ) ይጫወታሉ ( ካልተጫወቱ ስለሚያብዱ ) ይተኛሉ ( ካልተኙ ስለሚደክማቸው ) ያወራሉ (?) ውድ አንባቢ ሆይ ሌሊትህን በምን እያሳለፍህ ይሆን ? ለሞት ታናሽ ወንድም እንቅልፍ እየተሸነፍክ ? ወይስ ማንነትህን እየገነባህ ? ራስህን ተመልከት ….
ቅንድል መፅሔት ቅንነት ድል ያደርጋል ! ገጽ 26