ለ አእምሮ / Le'Aimero ለ አእምሮ የካቲት 2006 / February 2014/ እትም፣ ቅጽ 2 ቁጥር-07 | Page 17

ታምረኛው „ፎንቅስ“ /Phoenix/ በቁመናው ከሰጎን ይበልጣል። በጥንካሬው የዱር አራዊቶችን ያስፈራራል። በፍጥነቱ በምድር ላይ ማንም አይደርስበትም። አስፈላጊም ከሆነ እንደ መንኮራኩር አጓርቶ መሬቱን በሁለት የእግር ጥፍሮቹ ደብድቦ አንዴ ከተነሳ ጠፈርን በክንፉ ሸፍኖ በአንዴ ውቅያኖሱን አቋርጦ ሌላም አህጉርም በቀላሉ ይገባል ። አሉ ከሚባሉት ከአንደኛው የላባ ዘር ውስጥ ቢቆጠርም እንደ ሰጎኑ ይህን ፍጡር ከወፍ ወይም ከዶሮ ወይም ደግሞ ትልቅ ክንፍ ከአለው ከዱር አሞራ ዘር መድቦ እሱን መቁጠር ያዳግታዳል። በተፈጥሮው እሱን የሚያክልና የሚወዳደር በላባ ውበቱና በግርማ ሞገሱ በደማቃ የተለያዩ ቀለሞቹ ቅንብር -ተፈጥሮ በለገሰው ገጽታው ማንም ወፍ አይስተካከለውም። ቢደመሩም አይደርሱበትም። ይህ „ፎንቅስ“ የተባለውን ልዩ ስም ይዞ እዚህና እዚያ ታይቶ በተለያዩ አካባቢ የሚገኙትን ተመልካቾቹን ከተፍ ሲል በውበቱ አስደንግጦ አፍ የሚያስከፍተው ትልቁ አሞራ የጥንታዊ ዘመን ደራሲ ላክታንዝ የተባለው ጸሓፊ[i] – ሌሎቹም ስለ እሱ በዘመናቸው ጽፈዋል- እንደ እሱ ግን ተገርሞ በግሩም ቃላቶቹ አሳምሮ የጻፈ ሰው የለም።